መስቀል ማለት ምን ማለት ነው?

(ማቴ. 16:24-26)
ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና በቃል መነገሩ፣ በኅሊና መዘከሩ፣ በሰው ልብ መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ ከፍ ይበልና፣ ጌታችንንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ልጆቹ ፈቃዱን እያደረግን እንድንኖርና እርሱም ከመልካም ምግባራችንና ከበጎ ትሩፋታችን ብቻ የተነሳ ፍጹማን እንደማንሆን ያውቃልና፣ ከማያልቅ ልግስናው ከማይጓደል ምሕረቱ ዘመናትን እየመጸወተን ደስ የሚሰኝበትን ለእኛ እያደረገ በቸርነቱ ያኖረናል:: ከእርሱና ከዓላማው ጋር ጸንተን እንድንኖርም እንዲህ ሲል በቅዱስ ወንጌል አዝዞናል:: “ዘይፈቅድ ይትልወኒ ይጽላዕ ነፍሶ ያጥብዕ ወይንሳዕ መስቀለ ሞቱ ወይትልወኒ (እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ) ወምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኩሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ኃጉለ (ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?)” (ማቴ. 16:24-26)።
ጥንቱንም ቢሆን እኛ የተፈጠርነው በሕይወት እንድንኖር ነው። ትንሳኤና ሕይወት ክርስቶስ ግን የተወለደው ስለኛ እንዲሞት ነው:: በዚህም ሁላችን ለእርሱ እንድንኖር እርሱ ስለ ሁላችን ሞተ "በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። "(1ቆሮ፣ 5:15)። ይህ ግን መስቀል የገደለው ያይደለ ይልቁንም በመስቀሉ ሞትን ገደለበት እንጂ:: "በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።" (ፊል. 2:8) እንዲል::
ሊከተለኝ የሚወድ ነፍሱን ይጥላ አለ፣ ይህም ነፍሱንና ሥጋውን የሚለይ መከራ ለመቀበል ይጨክን ሲል ነው። ሰውስ ለክርስትና ፍኖቱ ለነፍሱ ሥምረት እያደረ የሥጋውን ፈቃድ እየገፋና እየጠላ ሊኖር ይገባዋል። ለዚህም ጌታችን ተከታዩን ሃሳብ እንዲህ ሲል አስፍሮታል "ወምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኩሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ኃጉለ፤ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?" መከተሉም ቢሆን ሌጣውን ያይደለ የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይለናል::
መስቀል ምንድር ነው ?
መስቀል በቀደመው ዘመን ለኃጢአተኞች እግዚአብሔርን ለበደሉ መቅጫ የነበረ "በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና" (ዘዳ፣21:23)። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ለክርስቲያኖች ኃይል፣ ጽንዕ፣ ቤዛና መድኃኒተ ነፍስ ሆኖ የሚያገለግል አርማ ነው:: ወደዚህ ክብር እንዴት ሊሻገር እንደቻለ ሊያስረዱ የሚችሉ በመስቀሉ ከተፈጸሙ ድንቅ መንክራት እፁብ ተዓምራት መካከል ተከታዮቹን ሦስት ዓበይት ነጥቦች እንደእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እንመለከታለን::
+ ጠላት የራቀበት ነው።
መስቀል የቀደመው እባብ የዲያቢሎስ ራስ የተቀጠቀጠበት እኛም ድል መንሳትን በግልጥ ያየንበት እጸ መድኃኒት ነው:: "በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ (በመስቀል) እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።" (ቆላ፣ 2:14) እንዲል።
+ እኛ የቀረብንበት ነው።
ተመልከቱ ራሱን ወደኛ ያቀረበበት ነው አላልንም "አመ ተለአልኩ እምድር እስህብ ኩሎ ኃቤየ፤ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።" (ዮሐ፣12:32) እንዳለ እኛን ወደራሱ አቀረበበት፣ ምክንያቱም ሰው በድሎ ራቀው እንጂ እርሱ ከሰው የተለየበት ጊዜ አልነበረምና። "እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም።" (ኤር፣23:23) እንዳለን። ይበልጡንም ለተዛምዶ ረቂቅ ቅርበቱ ያይደለ ሥጋችንን ነስቶ አማኑኤል ተሰኝቷል። "እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ።" ይህም በኩነት ታዲያ ዓላማው ወደእኛ መቅረብ ብቻ ቢሆን ይህ ልደቱ በበቃው ነበር። መስቀሉ ግን ወደኛ መምጣቱን ባንቀበል ወደራሱ ሊወስደን ወደ ሰማይ ቤታችን ሊስበን በቀራንዮ ተተከለ። ለዚህም ሊቁ ማር ኤፍሬም "አቅረበነ ኃቤሁ ዘዚአነ ሞተ ነሳ ወእንቲአሁ ሕይወተ ወኃበነ- ወደራሱ አቀረበን የእኛን ሞት ወስዶ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን" ሲል መነሻችንን ያስረዋል።
+ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት
ሰው የሞትን እጽ ቆርጦ ቢበላ አምላኩን በደለ። በዚህም የጸብ ግድግዳ ተተከለ። ሰው ከአምላኩ ተለየ ልዑለ ቃል ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ "ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል።" (ኢሳ፣59:2) ሲል እንደገለጸው፣ ታዲያ ከህገ ልቡና ወደ ህገ ኦሪት መሻገሩ ፍጻሜ ያለው ድኅነት ሊያመጣ ባለመቻሉ የሚበልጥና የሚሻል አዲስ ኪዳን የሚሰጥበት አዲስ መስዋዕት የሚሰዋበት አዲስ ድንኳን አስፈለገ (ዕብ፣ 9:11)። ለዚህም የአዲስ ኪዳን ሥርዓት ክቡር ደሙ የፈሰሰበት የሕይወት ህብስት ቅዱስ ሥጋው የተቆረሰበት ዐረፍተ ማእከል የተናደበት እጸ መድኃኒት ቅዱስ መስቀሉ ተሰጠን። "እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።" (ኤፌ፣ 2:15)።
እንግዲህ በጠቅላላው መስቀል የምንለው፣ በቁሙ ከቤተክርስቲያን ጉልላት እስከ ምዕመናን ንቅሳት የሚታይ የድል ምልክት፣ በሰሌዳ ተስሎ በጣት ተመሳቅሎ የሚገኝ የድኅነት አርማ፣ ካህናት በእጃቸው ይዘው የሚፈቱበት፣ ክርስቲያኖች በአንገታቸው አስረው ማንነታቸውን የሚመሰክሩበት መገለጫ ሲሆን. በሌላ አገባብ መከራ የተጋድሎ ፍኖት ማለት ነው።
እግዚአብሔር ወልድ ክርስቶስ ስለሁላችን መዳን መከራን ተቀብሎልናል። እናስተውል፣ እያንዳንዳችን በመዳን ኑሮ ሐሳባችን፣ እቅድ ምኞታችን በመከራው ልንካፈለው፣ በሞቱ ልንመስለው ፈለጋውን ልንከተለው ይገባናል።
"ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ። "(ዕብ፣13:12) እንደተባለ፤ ከበር ውጪ አለ በቀራንዮ ኮረብታ የራስ ቅል በተባለ ጎልጎታ ሊቀድሰን ተሰቀለ። እኛ ክርስቶስ በደረሰበት መከራ ከድቅድቁ ጨለማ ድንቁርና ወደሚደነቀው ብርሃን እውቀት የተሻገርነው፣ ስለ አዳም በደል መከሰስን ጥለን ስለራሳችን ጽድቅ መከራን በመቀበል እንድንከተለው ነው:: ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ "የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። "(1ኛ፣ጴጥ.2:21) ሲል እንዳስረዳን። በዚህም ኅሩይ ነዋይ ቅዱስ ጳውሎስ "እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ። "(ፊል.3:10-11)። ሲል ምኞቱን አስረዳን ምን ይጠቅማል? የሚል ቢኖር ልሳነ ዕፍረት እንዲህ ያስረዳዋል "ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።" (ሮሜ. 6:5)።
ሁሉ የራሱ መስቀል አለው ሸክሙን የሚሸከምበት
"ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።" (ሉቃ፣9:23)
ሁሉ የራሱን ሸክም ይሸከማልና
"ወኩሉ ያመክር ምግባሮ (ሁሉ ሥራውን ይመርምር ለሌላው ሳይሆን ለራሱ የሚመካበትን) እስመ ኩሉ ፆሮ ይፀውር (እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና)" (ገላ6:5) እንዲል።ስለዚህ የምንሸከመው መስቀላችን የምንሰቀልበት ሳይሆን ሸክማችንን የምንሰቅልበት ነው::"የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።" (ገላ፣ 5:24) እንደተባለ።
እስኪ አእምሮአችንን ከመባከን ሰብስበን ነፍሳችንን የሚያሳርፍ አንድ ታሪክ እናንብብ
"እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና። ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው።ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው።እርሱም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው።ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና። አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው።ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ።" (ማር 10:17)። አይገርማችሁም በምድራችን ላይ ገንዘብን መውደድ የከበደ ሸክም እየሆነባቸው "ገፋኤ-ነዳይ መፍቀሬ- ነዋይ" መጠርያቸው የሆኑ ብዙዎች አሉ:: ፍቅረ ነዋይ (ገንዘብን መውደድ) ለኃጢዓት ሥርና ራስ ነው ...... ጌታችን ተርቦ ሳይሳሳ፣ ተፈትኖ ድል ሳይሆን፣ ለሁላችን አርአያ በሆነበት ገዳመ ቆሮንቶስ ጠላታችንን ድል ከነሳባቸው መንገዶች አንዱ ፍቅረ ነዋይን በጸሊዓ ነዋይ ነበር። ይህም ፍቅረ ነዋይ ርዕሰ-ኃጣውእ ከስስትና ከትዕቢት ጋር አርዕስተ ኃጥውእ እየተባለ ይጠራል። ይሁንና ግን ከአስራ ሁለቱ አንዱ በሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ ልብ ገብቶ ተሳካለት። በዚህ ሥፍራ ደግም የኃጢዓት ሥር ተብሎ ተጠራ "ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።" (1ኛ.ጢሞ.6:10) እንዲል። እንግዲህ ይህን የመሰለው ኃጢዓት ሁሉ ክቡድ ሸክም ይባላል። የምሕረት አምላክ ግን በፍቅር ልሳን እንዲህ እያለ ይጠራናል "እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።" (ማቴ.11:28-30)።
ቀሊል የሆነውን የእርሱን ሸክም እንሸከም ዘንድ እሱ የኛን ክቡድ ሸክም በመስቀል ላይ ተሸከመ:: እንግዲህ ተመልከቱ በዚህ መንገድ እኛም ሕይወታችንን እንድንሰጠው ሕይወቱን ሰጠን ለምን? የሚል ቢኖር እርሱ የብዙዎችን ኃጢዓት በእንጨት ላይ የተሸከመው ብዙዎች የእርሱን ሕይወት በዘመናቸው እንዲሸከሙ ነውና:: ነቢዩ አስቀድሞ በትንቢት እንዲህ እንዳለ "ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።" (ኢሳ 53:12) ሊቀሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም የቃሉን መፈስጸም እንዲህ ሲል እንዳስረዳ "ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤" (1ኛ.ጴጥ፣2:24)።
መከራን መቀበል (መስቀላችንን መሸከም)
+ ኃጢዓትን (አርእስተ ኃጣውእ) ያስተዋል።
"በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና።" (1ጴጥ፣ 4:2)።
+ ወደ እግዚአብሔር ያስገባል።
"ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል" (ሐዋ 14:22) እንደተባለ ለብዙዎች ዘለፋ የሆነው ይህ የቅዱሳን ሐዋርያት ምስክርነት "በጸጋ ድነናል" እያሉ ባልተገባ ፍካሬ ቃሉን እየጠቃቀሱ፤ ለመብልና መጠጥ ይህን ለመሰለው የሥጋ ፈቃድ ራሳቸውን ለሚያስገዙ ጅራፍ ይሆንባቸዋል፤ ምክንያቱም "የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።" (ሮሜ.14:17) ይለናልና::
ማጠቃለያ
ቅዱስ አባታችን ብጹዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በአንድ መጽሐፋቸው "ፈተና ያለው ትምህርት ቤት አይደለም፣ ይልቁንም ትምህርት ቤት ያለው በፈተና ውስጥ ነው" ብለዋል። እኛም እንዲህ እንላለን "ሕይወት በመከራ የተሞላ ነው ለሚል፣ የለም ለክርስቲያንስ መከራ በህይወት የተመላ ነው እንጂ"፤ ሊቁ "መከራ ኢርኅቀ እምርዕሰ ጻድቃን ወርዕሰ ጻድቃን ኢርኅቀ እምነ መከራ ግሩም." ሲል ቅኔውን ይጀምራል። የማይጠፋ ስምና የሕይወትን አክሊል ገንዘብ ሊያደርጉ ሲሹ መከራ አይርቃቸውም። ቢርቃቸውም እንኳ እነርሱ ከመከራ መች ይርቁና። መክበርያቸውን ሽተው ራሳቸው ላይ ተጋድሎ ያጸናሉ ሌላውም ሊቅ የጸናውን ሰማዕት ተመለከተና "ኦ ጊዮርጊስ ስቃየ ኮንከ ለሥቃይከ" ሲል አደነቀ እንዴት ባለ መከራ እንዲገድሉት ይጨንቃቸው የነበሩ አላውያን ቢፈጩት፣ ቢያቃጥሉት፣ አመድ አድርገው ቢበትኑት "እነሆኝ የክርስቶስ ባርያ" እያለ ሞትን ድል ቢነሳና ከመካከላቸው ቢገኝ ለስቃዩ ስቃይ ሆነበት ወይግሩም! ታዲያ የቀደሙ ምስክሮች ሕይወት ይህ ከነበረ የእኛ ተጋድሎ ወዴት ይሆን? "ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?" (1ኛ.ጴጥ.4:18)።
እንግዲህ በሁሉ እናመስግን በፈተናችን ዋጋ በመከራችን ጸጋ እንድንቀበል እያሰብን ይህን እንጸልይ "ኦ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ አአኩተከ በእንተ ኩሉ ግብር ዘአምጻእከ ላዕሌየ እመሂ ረኃበ አው ጽጋበ እመሂ ጥኢና አው ደዌ እመሂ ፍሰሐ አው ኃዘነ...ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በእኔ ላይ ስላመጣህብኝ ነገር ሁሉ አመሰግናለሁ ረሃብ ቢሆን፣ ጥጋብ ጤንነት ቢሆን፣ ደዌ ደስታም ቢሆን ኃዘን"( ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ)።
መስቀሉን የሚሸከም ምረረ ገኃነምን ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን እየተዘከረ በመከራው ይደሰታል እንጂ አይማረርም። የጌታችን ወንድም የተሰኘ ራሱን የክርስቶስ ባርያ እያለ የጠራ ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ የመጀመርያ ምዕራፍ ቁጥር 2 እና 3 ላይ "ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት" ይለናል እኛም ከሐዋርያው ጋር እንዲህ እንላለን "ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።" (ሮሜ፣ 8:18)።
+++ ከፍኖተ መስቀሉ ከህያው ቅዱስ ቃሉ በረከት ይክፈለን። +++

Comments

Popular posts from this blog

የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል። መዝሙር ፻፲፩፥፮

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም

ዘመነ ፍሬ› ደግሞ ‹የፍሬ ወቅት፣ የፍሬ ዘመን፣ የፍሬ ጊዜ›