ናፍቆቴ ነበርሽ…
የዘመን ድልድዬ … ተስፋ እየመገብሽኝ
ጣዕምሽ አልባሴ ….. ፍቅርሽ ኑሮ ሆነኝ፡፡
በኑሮሽ ታዛ ስኖር ተጠግቼ
ረሃብ ጠግቤ በጥማት ረክቼ
እያለምኩሽ ነበር ገላሽን ጓጓቼ፡፡
እድሜን የሚያረዝመው የገላሽ ውበቱ
ክንድን የሚያፋፋው የሚፋጅ ሙቀቱ
ንጉስ ከናሽከሩ እተቧጠረ ይታደስበታል
ክብርሽ በየአልጋው እየተደፈረ ተጋልጦ ይታያል
ያቀፈም የተኛም ለገላሽ ዘብ ሁኖ ይዋደቅለታል፡፡
አይኔ እስኪጨልም፣ የምኞት ባዘቶ አቅሌን እስኪሰውር
ምላሴ ተቧጦ አፌ እስኪዘጋ እጄ እስኪቆረጥ እግሬ እስኪታሰር
ናፍቆቴ ስለሆንሽ ህልሜን አንቺ አደረኩ አብሬሽ ለመኖር፡፡
ለፍኩት ገላዬ ለደረቀ ጠጉሬም ህልሜን እየቀባሁ
የወየበ ቆሽቴን የታጠፈ አንጀቴን በተስፋሽ እያሰርሁ
መኖርሽ ‘ዳይጠፋ ውበትሽ እንዳይከስም ወዜን ቀባሻለሁ፡፡
እኔ ብዙ ስሆን የገላሽ ባይተዋር ቀንሽን ‘ምቆጥር
‘ሚተኛሽ አንድ ነው ሙቀትሽ ያፋፋው ቀኔን የሚቆጥር
አንዱ … ክብር ይቆፍራል፣ እድሜውን ያረዝማል
ብዙው … ክብርሽን ይሞላል፣ እድሜውን ይቆርጣል፡፡
አሁን ግን ናፍቆቴ……
ትዝታሽ በዛና ከናፍቆትሽ ቀድሞ በቁም አፈዘዘኝ
የገላሽ ውልብታ ያብሮ መኖር ትልሜ ዛሬ አይታየኝ
ምነው ባላወኩሽ የልጅነት ፍቅሬ እናቴ በቅታልኝ
አፌ ከተዘጋ ዐይኔም ከሟሟ ጣቴም ከተለየኝ
እግሬ ከታሰረ ህልሜን ከተቀማው እእምሮ ከራደኝ
አሁን ትዝታ ነሽ ድልድይ ሁነሽልኝ ዘመን ‘ማታሳዪ
አሁን ትዝታ ነሽ ኑሮዬን ልታድሽ ጥላቻ ‘ምትሞዪ
ተስፋን ‘ዳትግችኝ ሰውነቴ ጠፍቶሽ ከተኛሽ ‘ምትደክሚ
በናፍቆቴ መግል ወዜን እየጠባሽ የምታገግሚ፡፡
ዳሩ….
እኔ ብዙ የሆንኩ መቀመጤ ስቃይ መሄዴም ያቆስላል
አንድ የሆነ እርሱ መኖሬን ሲያጨልም ናፍቆቴን ሰውቷል፡፡
Comments
Post a Comment