ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል ሦስት (የመጨረሻ ክፍል)

ሱባዔ በዘመነ ሐዲስ
በዘመነ ሐዲስ በሰፊው የሚወሳው ሱባዔ ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ ፩ – ፲፬ ቀን ድረስ የገቡት ሱባዔ ነው፡፡ ይህ ሱባዔ ተሰውሮ የነበረውን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ተረድተው በረከቷን ለመሳተፍ አብቅቷቸዋል፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ጋር፣ ዐሥራ አምስት ዓመት በወንጌላዊው በዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩  ቀን ዐርፋለች፡፡ በሐዋርያት ውዳሴ፣ ዝማሬና ማኅሌት ነሐሴ ፲፬ ቀን ከተቀበረች በኋላ ነሐሴ ፲፮ ተነሥታ በይባቤ መላእክት ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ ‹‹ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ በሰማይም ከልጅዋ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች፤›› በማለት ወደ ሰማይ ማረጓንና በክብር መቀመጧን ተናግሯል፡፡ ከሺሕ ዓመት በፊትም አባቷ ዳዊት ‹‹በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች›› ሲል የተናገረው ትንቢት ይህንኑ የእመቤታችንን ክብር የሚመለከት ነው (መዝ. ፵፬፥፱)፡፡
‹ፍልሰት› የሚለው ቃል የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፣ በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው (ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ፣ ገጽ 68)፡፡ ለሐዋርያት የእመቤታችን የዕረፍትና የዕርገት ምሥጢር የተገለጠላቸው በሱባዔ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታ ወይም የሐዋርያት ሱባዔ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በቤተ ክርስቲያን ይታሰባል፡፡ ምእመናን የተቻላቸው ከሰው ርቀው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ያልተቻላቸው ደግሞ በአጥቢያቸው የውዳሴዋና የቅዳሴዋን ትርጕም ይሰማሉ፤ በሰዓታቱና በቅዳሴው ሥርዓት ይሳተፋሉ፡፡ በእመቤታችን አማላጅነት፣ በልጇ ቸርነት በምድር ሳሉ በሃይማኖት ጸንተው ለመኖር፤ በኋላም ለመንግሥቱ እንዲያበቃቸው እግዚአብሔርን ደጅ ይጠናሉ፡፡
የሱባዔ ዓይነቶች
፩. የግል ሱባዔ (ዝግ ሱባዔ)
የግል ሱባዔ አንድ ሰው ብቻውን ኾኖ በቤትና በአመቺ ቦታ የሚይዘው ማንም ሰው ሳያየው በግሉ የጸሎት በዓቱን ዘግቶ በሰቂለ ሕሊና ኾኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየውና እንዲሰማው በኅቡዕ የሚፈጽመው ሱባዔ ነው (ማቴ. ፮፥፭-፲፫)፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ አንድ ሰው ሱባዔ ሲገባ ዘጋ ይባላል፡፡ ዝግ ሱባዔ የያዘ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ይዞ ወደ በዓቱ ከተከተተ በኋላ ሱባዔው እስኪፈጸም ድረስ ከሰው አይገናኝም (መዝ. ፻፩፥፮-፯)፡፡
፪. የማኅበር ሱባዔ
የማኅበር ሱባዔ የሚባለው ካህናት፣ ምእመናን ወንዶችና ሴቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአንድነት ኾነው በቤተ ክርስቲያንና አመቺ በኾኑ ቦታዎች ዅሉ ተሰባስበው የሚገቡት ሱባዔ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር ቤት በመሔድ ይጸልዩ ነበር (፩ኛ ሳሙ. ፩፥፩፤ መዝ. ፻፳፩፥፩፤ ሉቃ. ፲፰፥፲-፲፬)፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የሐዋርያት ተከታዮች የኾኑ መነኮሳት፣ ካህናትና ምእመናን በገዳማት፣ በአድባራት፤ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ የጽዋ ማኅበርተኞች ስለ ማኅበራቸው ጥንካሬና ከማኅበርተኞቹ መካከል አንዱ ችግር ሲገጥመው የማኅበር ሱባዔ ይይዛሉ፡፡
፫. የዐዋጅ ሱባዔ
የዐዋጅ ሱባዔ በአገር ላይ ድንገተኛ አደጋ፣ አባር ቸነፈርና ጦርነት ሲከሠት፤ እንደዚሁም ለማኅበረ ምእመናን አስጊ የኾነ መቅሠፍት ሲመጣ፤ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሱባዔ የነነዌ ሰዎችና በፋርስ በስደት ይኖሩ የነበሩ እስራኤላውያን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ድረስ ለሦስት ቀናት ከመብል ከመጠጥ ተከልክለው በመጾም በመጸለያቸው እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት መልሶላቸዋል፡፡ ሌላው በፋርስ በስደት ይኖሩ የነበሩ አይሁድ በአስቴር ትእዛዝ የያዙት ሱባዔ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚያን ዘመን አይሁድ በያሉበት እንዲገደሉ አርጤክስስ በማዘዙ ከዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ለመዳን አይሁድ በዐዋጅ ሱባዔ ገብተዋል፡፡ አስቴር ገብታ ንጉሡን ስታናግረው ሌላው ሕዝብ በውጭ ዐዋጅ ዐውጀው ሱባዔ ገብተው ፈጣሪያቸውን ተማጽነዋል (አስቴር ፬፥፲፮-፳፰)፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያም ይህን የመሰለ የዐዋጅ ሱባዔ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ተደርጓል፡፡ ፋሽስት ጣልያን አገራችንን በመውረር ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ድንበሯን አልፎ በመጣበት ወቅት ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ‹‹ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ ርዳኝ›› በማለት የዐዋጅ ሱባዔ መያዛቸው ይነገራል፡፡ በዚህም መሠረት በየገዳማቱ ምሕላ ተይዟል፡፡ ንጉሡም ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ዓለምን እጅግ ባስደነቀ መልኩ ጥቁሮችን ለነጻነታቸው እንዲነሣሡ የሚያስችል ፋና ወጊ የኾነ ድል አግኝተው አገራችንን ለቅኝ ግዛት ያሰበውን ፋሽስት ጣልያንን ማሸነፋቸው በከፍተኛ ስሜት የምናስታውሰው ታሪክ ነው፡፡
የሱባዔ ቅድመ ዝግጅት
ሱባዔ መግባት የሚፈልግ ምእመን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ያለምንም ዝግጅት ሱባዔ መግባት ለፈተና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ (ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ)፣ ጊዜ ሱባዔ (በሱባዔ ጊዜ) እና ድኅረ ሱባዔ (ከሱባዔ በኋላ) ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
ቅድመ ሱባዔ (ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ)
በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት አለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይኾን ሱባዔ ቢገባ ከሱባዔው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ድካሙ ዋጋ ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባዔ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሐ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነውና፡፡ ከዚህም ባሻገር በአባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርጉልናል፡፡ ስለኾነም ቅድመ ሱባዔ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ተገቢ ነው፡፡
ለምሳሌ አንድ ሰው በሱባዔ ወቅት ልዩ ልዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙት የተሰጠውን ምክር በመጠቀም ፈተናውን ለመቋቋም ይችላል፡፡ እንደዚሁም የንስሐ አባቱ በሱባዔ ወቅት በጸሎት እንዲያስቡት መማከር ከአንድ ምእመን ይጠበቃል፡፡ ሱባዔ ለመግባት ስናስብ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሱባዔ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡ እንደ ዓቅማችንና እንደ ችሎታችን መጠን ከዚህ ቀን እስከዚህ ብለን በመወሰን ሱባዔ መግባት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖረው አንድ ሰው በዋሻ እዘጋለሁ ቢል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሱባዔ ወቅት ፈተና ስለሚበዛ የሚመጣበትን ፈተና መቋቋም ባለመቻሉ ሱባዔውን ሊያቋርጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ ዓቅምንና ችሎታን አገናዝቦ መወሰን ተገቢ ነው፡፡
ሌላው ቅድመ ሱባዔ ለሱባዔ ተስማሚ የኾነ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ሱባዔ የሚገባው አጽዋማትን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንገባበት ወቅት የጾም ወቅት መኾን አለመኾኑን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በአጽዋማት ወቅት የሚያዝ ሱባዔ ለተሐራሚ ጠቀሜታው እጅግ የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም በአጽዋማት ወቅት ብዙ አባቶች ሱባዔ ስለሚይዙ ከአባቶች ጸሎት ጋር ልመናችንና ጸሎታችን ሊያርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወቅትን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ ላይ ከወርኃ አጽዋማት ውጭ ሱባዔ አይያዝም ለማለት አይደለም፡፡ አንድ ሰው ፈተና ከአጋጠመው በማንኛውም ጊዜ ሱባዔ ሊገባ ይችላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሱባዔ የምንይዝበትን ቦታ መምረጥ አለብን፡፡ ለሱባዔ የምንመርጣቸው ቦታዎች ለፈተና የሚያጋልጡ መኾናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ሱባዔ ከተገባ በኋላ ሕሊናችን እንዳይበተን እገዛ ያደርግልናል፡፡ ጫጫታና ግርግር የሚበዛበት ቦታ በሰቂለ ሕሊና ለመጸለይ አያመችም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንይዝባቸው ቦታዎች ከከተማ ራቅ ያሉ ገዳማትና አድባራት ቢኾኑ ተመራጭ ነው፡፡
ጊዜ ሱባዔ (በሱባዔ ጊዜ)
በጸሎት ሰዓት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ፣ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንደዚሁም ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መቆም ወዲያና ወዲህ፣ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ አለመዟዟር፤ በሰፊሐ እድ፣ በሰቂለ ሕሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል (መዝ. ፭፥፫)፤ መዝ. ፻፴፫፥፪፤ ዮሐ. ፲፩፥፵፩)፡፡ በመጨረሻም ሱባዔ የገባ ሰው ሱባዔውን ሳይጨርስ ወይም ሱባዔውን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ መገናኘት የለበትም፡፡
ድኅረ ሱባዔ (ከሱባዔ በኋላ)
ለቀረበ ተማኅጽኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ላቀረብንለት ምልጃና ጸሎት እንደ ልባችን መሻት፣ እንደ እርሱ ቸርነት እርሱ በወደደ ጊዜ ያደርግልናል፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኘው የሕሊና ሰላምን ነው፡፡ ይህም ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባዔ ገብተን ያሰብነውን ካላገኘን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት መጽናትና መማጸን ይኖርብናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

Comments

Popular posts from this blog

የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል። መዝሙር ፻፲፩፥፮

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም

ዘመነ ፍሬ› ደግሞ ‹የፍሬ ወቅት፣ የፍሬ ዘመን፣ የፍሬ ጊዜ›