ዘመነ ፍሬ› ደግሞ ‹የፍሬ ወቅት፣ የፍሬ ዘመን፣ የፍሬ ጊዜ›

ዘመነ ፍሬ
የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! በክፍል ሰባት ዝግጅታችን አምስተኛውን የክረምት ንዑስ ክፍል (ቅዱስ ዮሐንስን) የሚመለከት ትምህርት ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ስድስተኛውን ክፍለ ክረምት (ዘመነ ፍሬን) የሚመለከት ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ እንድትከታተሉን መንፈሳዊ ግብዣችንን አስቀድመናል፡፡ መልካም የንባብ ጊዜ ይኹንላችሁ!
ከመስከረም ፱ – ፲፭ ቀን ያለው ስድስተኛው ክፍለ ክረምት ‹ፍሬ› ይባላል፡፡ ‹ዘመነ ፍሬ› ደግሞ ‹የፍሬ ወቅት፣ የፍሬ ዘመን፣ የፍሬ ጊዜ› ማለት ሲኾን ይኸውም ልዩ ልዩ አዝርዕት በቅለው፣ አድገው፣ አብበው ለፍሬ የሚደርሱበት፤ የሰው ልጅ፣ እንስሳትና አራዊትም ጭምር የዕፀዋቱን ፍሬ (እሸት) የሚመገቡበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚቀርቡ ምንባባትና ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር የሚዳስሱ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ምድርን ከፈጠረ በኋላ በጥፍር የሚላጡትን (ሎሚ፣ ሙዝ፣ ትርንጎ፣ ወዘተ)፤ በማጭድ የሚታጨዱትን (ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ወዘተ)፤ በምሳር የሚቈረጡትን (ወይራ፣ ዋርካ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ወዘተ)፤ የገነት ዕፀዋትን ፈጥሯል፡፡ እነዚህም በራሳቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ስንዴ፣ገብስ፣ ጤፍ፣ ወዘተ)፤ በጎድናቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ማሽላ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ ወዘተ)፤ በውስጣቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ዱባ፣ ቅል፣ ወዘተ)፤ በሥራቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ሽንኩርት፣ ቀይ ሥር፣ ካሮት፣ ድንች፣ ወዘተ) ተብለው በአራት ይመደባሉ (ምንጭ፡- ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት ፩፥፮-፲፫)፡፡
ተፈጥሯቸውም እንደ ሰው ከአራቱ ባሕርያት ነው፡፡ ከነፋስ በመፈጠራቸው በነፋስ ያብባሉ፤ ያፈራሉ፡፡ ከእሳት በመፈጠራቸው እርስበርሳቸው ሲፋተጉ እሳት ያስገኛሉ (አንዳንዶቹ)፡፡ ከውኃ በመፈጠራቸው ፈሳሽ ያወጣሉ፡፡ ከአፈር በመፈጠራቸው ሲቈረጡ በስብሰው ወደ አፈርነት ይቀየራሉ፡፡ እኛ የሰው ልጆችም በተፈጥሯችን (በባሕርያችን) ከዕፀዋት ጋር እንመሳሰላለን፡፡ በነፋስ ባሕርያችን ፍጥነት፤ በእሳት ባሕርያችን ቍጣ፤ በውኃ ባሕርያችን መረጋጋት፤ በመሬት ባሕርያችን ትዕግሥት ወይም ሞት ይስማማናልና፡፡ በሌላ በኩል የአዘርዕት ከበሰበሱ በኋላ መብቀልና ማፍራት የትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ነው፡፡ አዝርዕት ከበሰበሱ በኋላ ፍሬ እንደሚያስገኙ ዅሉ ሰውም ከሞተ በኋላ ተነሥቶ እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይቀበላልና፡፡ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡ እንዲህ ሲል፤ ‹‹… የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል፤ ባለ መበስበስ ይነሣል፡፡ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፡፡ በድካም ይዘራል፤ በኃይል ይነሣል፡፡ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል …›› (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፵፪-፵፬)፡፡
አዝርዕት ተዘርተው ከበሰበሱ በኋላ በቅለው፣ አብበው በራሳቸው፣ በጎድናቸው፣ በውስጣቸውና በሥራቸው እንደሚያፈሩ ዅሉ እኛም በራስ እንደ ማፍራት ፈሪሃ እግዚአብሔርን፤ በጎድን እንደ ማፍራት እርስበርስ መደጋገፍንና መተሳሰብን፤ በውስጥ እንደ ማፍራት ንጽሕናን፤ በሥር እንደ ማፍራት ትሕትናን ገንዘብ ማድረግን ከዕፀዋትና ከአዝርዕት መማር ይገባናል፡፡ እንደዚሁም ዕፀዋት ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶና ከዚያ በላይ መልካም ፍሬ እንደሚያፈሩ በመልካሟ መሬት በክርስትና የተዘራን እኛ ክርስቲያኖችም ዘር የተባለውን የእግዚአብሔርን ቃል በሚገባ ተምረን ከወጣኒነት ወደ ማእከላዊነት፤ ከማእከላዊነት ወደ ፍጹምነት በሚያደርስ የጽድቅ ሥራ በመትጋት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ መፋጠን ይኖርብናል (ማቴ. ፲፫፥፳፫)፡፡
ዕፀዋት የሚሰጡት ፍሬ እንደየማፍራት ዓቅማቸው ይለያያል፤ ፍሬ የማያፈሩ፣ ጥቂት ፍሬ የሚያፈሩ፣ ብዙ ፍሬ የሚያፈሩ ዕፀዋት ይገኛሉ፡፡ እንደዚሁ ኹሉ ምእመናንም በክርስትና ሕይወታችን የሚኖረን በጎ ምግባር የአንዳችን ከአንዳችን ይለያል፡፡ ፍሬ የክርስቲያናዊ ምግባር እንደዚሁም የሰማያዊው ዋጋ ምሳሌ ነውና፡፡ በክርስትና ሕይወት ያለምንም በጎ ምግባር የምንኖር ኀጥአን ብዙዎች የመኾናችንን፤ እንደዚሁም ጥቂት በጎ ምግባር ያላቸው ምእመናን የመኖራቸውን ያህል በአንጻሩ ደግሞ በጽድቅ ላይ ጽድቅ፣ በመልካም ሥራ ላይ መልካም ሥራን የሚፈጽሙ፤ ከጽድቅ ሥራ ባሻገር በትሩፋት ተግባር ዘወትር ጸንተው የሚኖሩ አባቶችና እናቶችም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ይህን ዓይነት የክርስቲያናዊ ሕይወት ልዩነት ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፤ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል … ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል፤ ያበረክትላችሁማል፡፡ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል›› በማለት ይገልጸዋል (፪ኛ ቆሮ. ፱፥፮-፲)፡፡ ገበሬ በዘራው መጠን ሰብሉን እንዲሰበስብ ‹‹ለዂሉም እንደየሥራው ዋጋውን ትከፍለዋለህ›› ተብሎ እንደ ተጻፈው ክርስቲያንም በሠራው መጠን ዋጋውን ያገኛልና በጸጋ ላይ ጸጋን፣ በበረከት ላይ በረከትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይጨመርልን ዘንድ ዂላችንም መልካም ሥራን በብዛት ልንፈጽም ይገባናል፡፡ ‹‹… እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ፡፡ እነሆ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል፡፡ እናንተ ደግሞ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፡፡ የጌታ መምጣት ቀርቧልና›› እንዳለን ሐዋርያው (ያዕ. ፭፥፯-፰)፡፡
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ምድርኒ ወሀበት ፍሬሃ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች›› (መዝ. ፷፮፥፮፤ ፹፬፥፲፪) የሚለውን የዳዊት መዝሙርና ሌሎችንም ተመሳሳይ ኃይለ ቃላት ሲተረጕሙ ምድር በኢየሩሳሌም፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በምእመናን፣ በእመቤታችን፤ ፍሬ ደግሞ በቃለ እግዚአብሔር (በሕገ እግዚአብሔር)፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር፣ እንደዚሁም በጌታችን አምላካችን መድኂታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመሰል ያስተምራሉ፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ምድርኒ ወሀበት ፍሬሃ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች›› በሚለው ኃይለ ቃል ምድር የተባለች ኢየሩሳሌም የዘሩባትን እንደምታበቅል፤ የተከሉባትን እንደምታጸድቅ፤ አንድም ይህቺ ዓለም ፍሬን፣ አምልኮተ እግዚአብሔርን እንደምታቀርብ፤ ቤተ ክርስቲያን ወይም ምእመናን እግዚአብሔርን ሲያመልኩ እንደሚኖሩ፤ ከዚሁ ዂሉ ጋርም ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ተወለደ የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡ ‹‹ምድርኒ ወሀበት ፍሬሃ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች›› – ምድር ከተባለች ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍሬ የተባለው ክርስቶስ መገኘቱን ለማጠየቅም ቅዱስ ገብርኤል በሉቃስ ወንጌል የተናገረው ቃል ማስረጃ ነው (ሉቃ. ፩፥፳፰)፡፡ እኛም የመልአኩን ቃል መሠረት አድርገን በዘወትር ጸሎታችን ‹‹ቡርክት አንቲ እምአንስት ወቡሩክ ፍሬ ከርሥኪ፤ አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽ ፍሬም የተባረከ ነው›› እያልን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ለልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ውዳሴ እናቀርባለን፡፡
በማቴዎስ ወንጌል ፲፫፥፩-፳፫ ተጽፎ እንደምናገኘው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስትና ሕይወትን ከዘርና ፍሬ ጋር በማመሳሰል አስተምሯል፡፡ ይኸውም አንድ ገበሬ ዘር ሲዘራ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር ከመብቀሉ በፊት በወፎች እንደ ተበላ፤ በጭንጫ ላይ የተጣለውም ወዲያውኑ ቢበቅልም ነገር ግን ጠንካራ ሥር ስለማይኖረው በፀሐይ ብርሃን እንደ ጠወለገ፤ በእሾኽ መካከል የወደቀው ደግሞ ሲበቅል በእሾኽ እንደ ታነቀ፤ ከዂሉም በተለየ መልኩ በመልካም መሬት ላይ የተጣለው ዘር ግን አድጎ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ ፍሬ እንደ ሰጠ የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህም ምሳሌ አለው፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተረጐመው በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ክርስቲያን ምሳሌ ነው፤ ሙሉ እምነት ስለማይኖረው በመከራው ጊዜ አጋንንት ይነጥቁታልና፡፡ በጭንጫ ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል፣ ነገር ግን ተግባራዊ የማያደርግ ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ምእመን በጠንካራ እምነት ላይ የጸና አይደለምና በሃይማኖቱ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ፈጥኖ ይሰናከላል፡፡ በእሾኽ መካከል የተዘራውም ቃሉን የሚሰማ ነገር ግን በዚህ ዓለም ዐሳብና ባለጠግነት ተታሎ ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡
በመልካም መሬት የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ የሚተገብር ክርስቲያን ምሳሌ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምእመን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ይኖራል፤ መልካም ሥራም ይሠራል፡፡ በመልካም መሬት የተዘራው ዘር ስለ አንዱ ፋንታ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ እንደሚያፈራ ዅሉ በክርስቲያናዊ ግብር ጸንቶ የሚኖር ምእመንም ሥራውን በሦስት መንገድ ማለትም በወጣኒነት፣ በማእከላዊነትና በፍጹምነት ደረጃ እንደሚወጣ፤ ዋጋውንም በሥራው መጠን እንደሚያገኝ የሚያስረዳ ነው፡፡ አንድም ባለ መቶ ፍሬ የሰማዕታት፤ ባለ ስድሳ የመነኮሳት፤ ባለ ሠላሳ በሕግ ተወስነው በዓለም የሚኖሩ ምእመናን ምሳሌ ነው፡፡ በተመሳሳይ ምሥጢር ዂሉም የፍሬ መጠን በዅሉም ጾታ ምእመናን ሕይወት ውስጥ እንደሚስተዋል ሊቃውንት ይተረጕማሉ፡፡ ስለዚህም በሰማዕትነትም፣ በምንኵስናም፣ በዓለማዊ ሕይወትም ውስጥ የሚኖሩ ምእመናን መልካም ግብራቸው እጅግ የበዛ ከኾነ በባለ መቶ ፍሬ፤ መካከለኛ ከኾነ በባለ ስድሳ፤ ከዚህ ዝቅ ያለ ከኾነ ደግሞ በባለ ሠላሳ ፍሬ ይመሰላል (ምንጭ፡- ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ)፡፡
ከዚሁ ዂሉ ጋርም ዕፀዋት ለመጠለያነት የማይጠቅሙ እንደዚሁም ለምግብነት ወይም ደግሞ ለመድኀኒትነትና ለሌላም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚጠቅም ፍሬ የማያስገኙ ከኾነ ተቈርጠው ይጣላሉ፡፡ ምእመናንም ‹ክርስቲያን› ተብለን እየተጠራን ያለ ምንም በጎ ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት ከኖርን ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጪ እንኾናለን፡፡ ከኀጢአት ካልተለየን በምድር መቅሠፍት ይታዘዝብናል፤ በሰማይም ገሃነመ እሳት ይጠብቀናል፡፡ ይህን እውነት በመረዳት ዂላችንም በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ‹‹… ምሣር በዛፎች ሥር ተቀምጧል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ዂሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል›› (ማቴ. ፫፥፲) ተብሎ እንደ ተጻፈው ፍሬ የማያፈሩ ዕፀዋት በምሣር ተቈርጠው እንዲጣሉ እኛም ያለ መልካም ሥራ ከኖርን በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ፍርድ ከገነት፣ ከመንግሥተ ሰማያት እንባረራለን፡፡ ይህ ክፉ ዕጣ እንዳይደርስብን ከሃይማኖታችን ሥርዓት፣ ከቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ሳንወጣ የቅዱሳንን ሕይወት አብነት አድርገን ለጽድቅ ሥራ እንሽቀዳደም፡፡ ‹‹እንግዲህ እነዚህን የሚያኽሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ዅሉ ቶሎም የሚከበንን ኀጢአት አስወግደን የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን (ዕብ. ፲፪፥፩-፪)፡፡

Comments

Popular posts from this blog

የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል። መዝሙር ፻፲፩፥፮

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም