የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል። መዝሙር ፻፲፩፥፮
ባለንበት ዓለም ውስጥ ለሰው ልጆች ሕይወት ጠቃሚ የሆነ ሥራ የሠሩ ብዙ ሰዎች ይገኛሉ። እኛም ባልነበርንበት ጊዜ ለአለማችን እዚህ ደረጃ መድረስ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ታላላቅ ስመ ጥር የሆኑ ሰዎች በታሪክ ውስጥ አልፈዋል። እነዚህ ለዓለም ማሕበረሰብ ካበረከቱት አስተዋጽኦ አንጻር በሕይወት ሳሉ ብቻ ሳይሆን ከሞቱም በኃላ ስማቸው በታሪክ ማሕደርተጽፎ በየጊዜው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ሲዘከር ይኖራል። የሰሩትንም ሥራ ለትውልዱ በማስተዋወቅ በክብር በማስቀመጥ ትውልድ አርያነታቸውን እንዲከተል ለማድረግ በየጊዜው ታላቅነታቸው ሲነሳ ታሪካቸው ሲነገር መስማት በዓለም ታሪክውስጥ የተለመደ ነው።
በመንፈሳዊው ዓለም ደግሞ የእግዚአብሔር የሆኑ ሰዎች በዚህ ምድር ቆይታቸው «ሰውነቱን ሊያድናት የሚወድ ይጣላት ስለእኔ ሰውነቱን የጣላት ያገኛታል»ማቴ 10፥39 በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው ትምህርት መሰረት በኃጥአን ላይ የሚፈረድ ቅጣት፣ ለጻድቃን የሚሰጥ ዋጋ እንዳለ በመረዳት፣ ከምድራዊ ሕይወት ይልቅ ሰማያዊ ሕይወትን በመናፈቅ፣ ከኃላዬ ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ዕለት ዕለት ይከተለኝ የሚለውን አምላካዊ መመሪያ መሰረት በማድረግ ለተጋድሎ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ አሳልፈው የሰጡ ቅዱሳን በየዘመኑ መነሳታቸውን የቤተ ክርሰቲያን ታሪክ በወርቃማ ብዕር ታሪካቸውን ጽፎ የምናገኛቸው የቤተ ክርስቲያን ብሩሃን ከዋክብት መስተጋድላን ብዙ ናቸው።
እነዚህ ቅዱሳን ቅዱስ ጳውሎስ «ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ»ዕብ 11፥37 ብሎ የተናገረላቸው ቅዱሳን ናቸው። ይህችን ዓለም ኃላፊ ጠፊ መሆኑን አውቀውና ተረድተው ውበቷና ጣዕሟ ሳይማርካቸው ለዘላለማዊ ክብር ሲሉ ዓለምን ከነኃጢያቷ የናቁ እነርሱ በዓለም ዘንድ የሞቱ ዓለምም በእነርሱ ዘንድ የሞተች በመሆኗ ከእናት ከአባት፣ ከወንድም ከእህት፣ከዘመዶቻቸው ሁሉ ተለይተው በዱር በገደል የተንከራተቱ የቀን ሐሩር፣ የሌሊቱ ቁር፣ ሳያሰቅቃቸው በጾም በጸሎት ተወስነው ጸብአ አጋንንትን ግርማ ሌሊቱን ታግሰው ወርቅ በእሳት እንዲፈተን እነርሱም በመከራ ተፈትነው ያለፉ ናቸው። ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀናተኛ በመሆናቸው ከራሳቸው ሕይወት አልፈው ሌሎች ሰዎች ከዘላለማዊ ቅጣት ለመታደግ «እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለ አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ» ማቴ 5፥14_16 ብሎ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው መሰረት በጨለማ ላሉ ብርሃን ሆነዋል።
በአምልኮተ ጣዖት ውሰጥ ያሉ አህዛብን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ለመመለስ እሰካሉበት ድረስ በመሄድ ወንጌለ መንግስትን ሰብከዋል። የክርስቶስን የባሕሪ አምላክነት መስክረዋል። በዚህ የተነሳ የተሰጣቸውን መክሊት በማትረፍ ታማኝ አገልጋይ ለመሆን የበቁ በጥቂቱ ታምነው በመገኘታቸው ለብዙ ክብር ለመብቃት ችለዋል። ከእነዚህ ቅዱሳን መካከል አንዱ በምናኔ ሕይወት የሚታወቁትና ቤተ ክርሰቲያናችን በየዓመቱ ጥቅምት 5 ቀን በከፍተኛ ክብረ በዓል የምታስባቸው ጻድቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይገኙበታል።
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የትውልድ አገራቸው ግብፅ ነው። ወላጆቻቸው ፈሪሃ እግዚአብሔር የነበራቸው በጾም በጸሎት ሕይወታቸውን የሚመሩ ሕገ እግዚአብሔርን የሚጠብቁ ነበሩ። መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ እንዲል ጻድቁ አባት የተገኙት ከተቀደሰ ቤተሰብ ነው። «በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለው ከማህጸን ሳትወጣ ቀድሼሃለው» ኤር 1፥5 እንዲል ከእናታቸው ማህጸን ሳይወጡ ለታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ የታጩ አባት ለመሆን በቅተዋል።
ከህጻንነት እድሜያቸው ጀምሮ በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲታነጹ በግብፅ አገር በሚገኙ ታላላቅ ገዳማት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እየዞሩ ከታላላቅ መምህራን ዘንድ መንፈሳዊ ትምሕርትን ተምረዋል። በብሕትውናና በምናኔ ኑሮ ታላቅ ተጋድሎ በመፈጸም የእግዚአብሔር የክብር መግለጫ ለመሆን በቅተዋል። በመንፈሰ እግዚአብሔርም በመመራት ወደ አገራችን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኪደተ እግራቸው ምድሪቱን በመርገጥ ቀድሞ በተለያዩ ቅዱሳን ባገኘችው በረከት ላይ ሌላ በረከትን እንድታገኝ አድርገዋታል። በተለያዩ የአገሪቱ ከፍሎች በመዘዋወር ወንጌልን ሰብከዋል። አሕዛብ የነበሩትን በማስተማርና በማጥመቅ ክርስቲያን አድርገዋል። ከገቢረ ኃጢያት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል። «በእኔ የሚያምን እኔ የማደረገውን ሥራ ደግሞ እርሱ ያደርጋል ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል»ዮሐ 14፥12 ተብሎ እንደተጻፈ በእርሱ አምነውና ለእርሱ ታምነው ተሰማርተዋልና በስሙ ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራትን ፈጽመዋል። እውራንን አብርተዋል፣ መስማት የተሳናቸውን እንዲሰሙ አድርገዋል፣ ሙታንን አስነስተዋል፣ አጋንንትን ድል አድርገዋል።
በተለይም ዝቋላ ተብሎ በሚጠራው ተራራ ላይ ብዙ ተጋድሎን ፈጽመዋል። በአጋንንት ይደርስባቸው የነበረውን ልዩ ልዩ ፈተና በድል አድራጊነት በመወጣት መንፈሳዊ አርበኛ ለመሆን ችለዋል። በዚህ ሥፍራ ባደረጓቸው ታላላቅ ተጋድሎ ውስጥ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ እጃቸውን ዘርግተው በእንባ ጭምር አብዝተው ጸልየዋል። በመሆኑም ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ «የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች» ያዕ 5፥16 እንዲል በጸለዩት ጸሎት ባቀረቡት ምልጃ ምህረትን ከፈጣሪያቸው ዘንድ አሰጥተዋል። ጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ባደረጉት ተጋድሎ ፈጣሪያቸውን በማስደሰታቸው ከፈጣሪያቸው ዘንድ ቃል ኪዳን ተሰጥቷቸዋል። ይህም ቃል ኪዳን ዘላለማዊ ቃል ኪዳን በመሆኑ ለዘላለም የሚኖር ነው። «ሰንበቴን ለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ የማይጠፋ የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ» ኢሳ 50፥5-6ሲል እግዚአብሔር ራሱ ለቅዱሳን የገባው ቃል ኪዳን አለ።
በዚህም ቃል ኪዳን መሰረት «ነቢዩን በነቢይ ስም የሚቃበል የነቢዩን ዋጋ ያገኛል። ጻድቁን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም ያጠጣ እውነት እላችኋለው ዋጋው አይጠፋበትም»ማቴ 10፥40 እንዲል
ዛሬም በጻድቁ አባታችን ቃል ኪዳን በመታመን በረከታቸውን በመሻትቤተ ክርስቲያንን በስማቸው በማነጽ ነዋያተ ቅድሳት በማቅረብ መብዐ በማስገባት የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት በአማላጅነታቸው የሚጠቀሙ ብዙ ሰዎች አሉ።
እኛም በዚህ በተገባላቸው ቃል ኪዳን በመጠቀም አምላካችን በረድኤቱ እንዲጐበኘን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የጻድቁ አባታችን ረድኤት በረከት አይለየን። አሜን!
Comments
Post a Comment