እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐና የተሰጣቸው ጸጋ እጅግ ታላቅ ነበር።ታላቅነቱንም መፈክረ ሕልም እንደነገራቸው፡- በሕልማቸው እና ከቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ተረድተውታል። በመጽሐፍ ቅዱስ፡- እግዚአብሔር ፈቃዱን፡- ለአቤሜሌክ፥ ለያዕቆብ እና ለዮሴፍ በሕልም ገልጦላቸው እንደነበር ይታወቃል። ዘፍ፡፳፥፫፤ ፳፰፥፲፪፤ ፴፯ ፥፭።የእመቤታችን ጠባቂ ለነበረ ለጻድቁ ለዮሴፍ ደግሞ፡- ነገረ ማርያም ማለትም፡- እግዚአብሔር መርጦአት፥ ቅዱሳን ነቢያት ትንቢት ተናግረውላት፥ በመንፈስ ቅዱስ ግብር፡- በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የመውለዷን ነገር፥ ከዚያም በኋላ፡- ጌታን አዝላ የመሰደዷን እና ከስደት የመመለሷን ነገር፥ ቅዱሳን መላእክት በሕልም ነግረውት ነበር። ማቴ፡፩፥፳፤ ፪፥፲፫፣፲፱። (ነገረ ማርያምን እግዚአብሔር እንዲህ ካልገለጠልን በቀር፥ ጣዕሟ በአንደበታችን ፍቅሯም በልቡናችን ሊያድርብን አይችልም፤) ለዮሴፍ ወልደ ያዕቆብና ለነቢዩ ለዳንኤል ሕልም የመፍታት ጸጋ ተሰጥቶአቸው ስለነበረ፥ የነገሥታቱን ሕልም እንኳ እንደፈቱላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ቋሚ ምስክር ነው። ዘፍ፡፵፥፭፤ ፵፩፥፲፬፣ ዳን፡፪፥፳፭፤ ፬፥፬።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናቷ ማኅፀን እያለች አያሌ ተአምራትን በማድረጓ፥ ለቅዱስ ኢያቄምና ለቅድስት ሐና ከባድ ፈተና ሆኖባቸው ነበር።የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት ሰይጣን አይሁድን በምቀኝነት አስነ ሣባቸው።የምቀኝነት ምንጩ ደግሞ ክፉ ልቡና ነው፤ ማር፡፯፥፳፪። የሰው ልጅ መንፈሳዊነቱን ትቶ ፍጹም ሥጋዊ ሲሆን ምቀኝነት ይሰለጥንበታል። ገላ፡፭፥፳፩። ፈቃደ ሥጋው ገዝቶት በክፋትና በምቀኝነት የሚኖር ሰው ደግሞ ለማንም ፍቅር ሊኖረው አይችልም። ገላ፡፫፥፫። ሰይጣን አዳምን እና ሔዋንን ያሳሳተው በምቀኝነት ነው። ዘፍ፡፫፥፩። ቃየል አቤልን የገደለው በምቀኝነት ነው። ፬፥፰። ዔሳው ወንድሙን ያዕቆብን ለመግደል የዛተው በምቀኝነት ነው። ዘፍ፡፳ ፯፥፵፩። የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸውን ዮሴፍን፡- “እንግደለውና በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው፤” ያሉት፥ በኋላም በሮቤል በጎ ምክር አሳባቸውን ለውጠው ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች የሸጡት በምቀኝነት ነው። ዘፍ፡፴፯፥፳፣፳፰። ሄሮድስ፡- ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ያሳደደው፥ በዚህም ምክንያት አሥራ አራት እልፍ ሕፃናትን ያሳረደው በምቀኝነት ነው። ማቴ፡፪፥፲፮። አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን እጆቹን እና እግሮቹን በቅንዋተ መስቀል ቸንክረው የገደሉት በምቀኝነት ነው። ማር፡፲፭፥፳፬።
ምቀኝነት የባህርያቸው እስከሚያስመስልባቸው የደረሱ አይሁድ፥ በማኅፀነ ሐና ባለች ፅንስ ምክንያት የሚደረጉት ልዩ ልዩ ተአምራት አላስደሰታቸውም። ተሰብስበውም፡- “ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? ሐና ፀንሳ ሳለች በማኅፀንዋ ታድናለችና፥ የእስራኤልን መንግሥት አጥፍታ በእኛ ላይ ልትነግሥ አይደለምን?” ተባባሉ። ይኸውም፡- “ከአሁን ቀደም ከእነዚህ ወገን የሆኑት ዳዊት ሰሎሞን፥ አርባ፣ አርባ ዓመት ገዝተውን ነበር፥ ከእነዚህ የሚወለደው ደግሞ ምን ያደርገን ይሆን?” ብለው ነው። ሀገር ያወቀውን፥ ፀሐይ የሞቀውን ምቀኝነታቸውን በሃይማኖት ለመሸፈን፡- “በሙሴ ሕግ መሠረት በድንጋይ ቀጥቅጠን እንግደላቸው፤” ብለው በሌሉበት ሞት ፈረዱባቸው። ይህ የሙሴ ሕግ የሚጠቀሰው ለአመንዝሮች እንጂ፥ ትዳራቸውን አክብረው፥ ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው፥ በጾም በጸሎት ተወስነው በቅድስና ለሚኖሩ፥ ለቅዱስ ኢያቄምና ለቅድስት ሐና አልነበረም። ዘሌ፡፳፥፲፣ዘዳ፡፳፪፥፳፬።
መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ፥ የመፀነሷን ነገር አስቀድሞ በሕልም ነግሮአቸው የነበረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፥ እያዩት ከሰማይ ወርዶ፥ “በዘመድ የከበራችሁ ኢያቄምና ሐና ሆይ፥ ተነሡ፤” አላቸውና ወደ ሊባኖስ ተራራ ወሰዳቸው። ይህም፡- ቅዱሳን መላእክት ሎጥን ከሰዶም አውጥተው፥ “ወደዚያ ሸሽተህ አምልጥ፤” እንደ አሉት አይነት ነው። ዘፍ፡፲፱፥፳፪። የቅዱሳን መላእክት አማላጅነትና ተራዳኢነት ለእግዚአብሔር ሰዎች ሁልጊዜ እንዲህ እንደሚደረግላቸው አያሌ ማስረጃዎች አሉ። የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ዮሴፍን፡- “ሄሮድስ ሕፃኑን(ኢየሱስን) ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስከምነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ፤” ያለው ለዚህ ነው። ማቴ፡፪፥፲፫። የሞት ፍርድ ይጠብቀው የነበረውን ቅዱስ ጴጥሮስንም ሰንሰለቱን ፈትቶ፥ ወኅኒ ቤቱን ከፍቶ አውጥቶታል። እርሱም በቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት የሚያምን ስለሆነ፥ ወደ ልቡ ተመልሶ፡- “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ፤” ብሎአል። የሐዋ፡፲፪፥፩-፲፩። (የዘንድሮዎቹ ኢየሱስን እንስብካለን ባዮች ግን ይህን አያውቁም፤ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ትክክለኛ ኢየሱሳዊ ቢሆኑ ኖሮ፥ በቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት እና አማላጅነት እንደሚድኑ ያምኑ ነበር፤) ቅዱስ ጳውሎስም፡- በሥጋም በነፍስም የሚድኑትን ሰዎች ለመራዳት ቅዱሳን መላእክት እንደሚላኩ መስክሮአል። ዕብ፡ ፩፥፲፬። (እንደ ክረምት አግቢ የፈሉ ተሀድሶዎች ግን ይህን አይመሰክሩም፤) የባህርይ ስግደት የሚሰገድለት ጸሎት ተቀባይ ኢየሱስ ክርስቶስ፡- አብነት ሊሆነን በጌቴሴሚኒ በጸለየና በሰገደ ጊዜ፥ “ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታው መልአክ ታየው፤” ይላል። ሉቃ፡፳፪፥፵፫። በዚህም ለሥጋ ለባሽ በጠቅላላ ተራዳኢ መልአክ እንደሚያስፈልገው አስተምሮናል። (በስሙ የሚነግዱ የዛሬዎቹ ኢየሱሳውያን ግን ይህን ትምህርት አይተነፍሱም፤) በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ዘመን ያለ ተራዳኢ መልአክ እግዚአብሔርን ያገለገለ ሰው ማንም የለም። ነቢዩ ኤልሳዕ፡- ቅዱሳን መላእክት የእሳት አጥር ሆነው ሲጠብቁት አይቶአል፥ የጠላትን የሠራዊት ብዛት በማየት ፈርቶ የነበረ ሎሌውም በነቢዩ ጸሎት ተገልጦለታል። ፪ኛ፡ነገ፡፮፥፲፬-፲፯። ቅዱስ ዳዊት፡- “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል፤”ያለው ለዚህ ነው። መዝ፡፴፫፥፯።
ቅዱስ ገብርኤል፡- ቅዱስ ኢያቄምን እና ቅድስት ሐናን ወደ ሊባኖስ ተራራ የወሰዳቸው ያለ ምክንያት አይደለም። “ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ (ጥንተ አብሶ የተባለ የአዳም ኃጢአት ያላረፈብሽ ንጽሕተ ንጹሐን ነሽ፤) ነውር የለብሽም። (የአዳም ኃጢአት የለብሽም)። እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤” ተብሎ ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የተነገረው ቃለ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። መኃ፡፬፥፯። ሊባኖስ፡- ከገሊላ በስተ ሰሜን እና ከፊንቄ በስተ ምሥራቅ የሚገኝ ተራራማ ሀገር ነው። ዘዳ፡፩፥፯። በዝግባ ዛፍ የተሞላ ተራራ ነው፥ ንጉሡ ሰሎሞን ለቤተ መቅደሱ ሥራ ያስፈለገውን የዝግባ እንጨት ያስመጣው ከዚያ ነበር። ፩ኛ፡ነገ፡፬፥፴፫፤ ፭፥፮። ምሳሌነቱ ጥሩ ነው፥ ከሊባኖስ የተገኘ ዝግባ ለአግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆነ ሁሉ፥ በሊባኖስ የተወለደች ድንግል ማርያምም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆና ተገኝታለች። አንድም የሊባኖስ ዝግባ ለቅዱሳን ምሳሌ ነው፤ የዚያ ፍሬው እንዲበዛለት፥ እነርሱ ደግሞ ጸጋና ክብር ይበዛላቸዋል። መዝ፡፺፩፥፲፪።
ቅድስት ሐና የፅንስዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ ግንቦት አንድ ቀን፥ ከፀሐይ ይልቅ የምታበራ ሴት ልጅ ወለደች። “እመቤታችን ማርያም መልኳ እንደ አምላክ መልክ ነው፥ የአምላክን መልክ ይመስላል፤” እንዲል፡- የመልኳ ደም ግባት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነበር። መዓዛዋም ከሽቱዎች ሁሉ ይበልጥ ነበር። ዘመዶቿ እና ጐረቤቶቿም በሰሙ ጊዜ፥ ፈጽሞ ደስ አላቸውና ተሰብስበው ወደ እርሷ መጡ። ልጇንም ባዩ ጊዜ ፈጽመው አደነቁ፥ እርስ በርሳቸውም፡- “እንደዚህ ያለች ብላቴና ከቶ አይተን አናውቅም፤” ተባባሉ። ምልዕተ ጸጋ በመሆኗ የእግዚአብሔር ብርሃን በላይዋ ያበራ ነበር። “ከፀሐይ ይልቅ ትበሪያለሽ፤” የተባለችው ለዚህ ነው። በዚህ ምክንያት የብርሃን ድንኳኖች በሊባኖስ ተራሮች ላይ ተተክለዋል፥ ሠራዊተ መላእክት ከሰማይ ነጕደው መጥተዋል፥ ዝማሬያቸውንም አሰምተዋል። ቅድስት ቅዱሳን ናትና መዓዛ ቅዱሳን ተራራውን አውዶአል፥ “ዐጠንተ መንበሩ፤” እንዲል፡- የአምላክ መንበር ናትና ዐጥነዋታል። “ኢያቄም ወሐና ወለዱ ሰማየ፤” እንዲል፡- የተወለደችው ዳግሚት ሰማይ በመሆኗ ሰማያውያን መላእክት በእርስዋ ዘሪያ ተሰብስበዋል። ቅዱስ ያሬድ፡- “ከሰማያት በላይ ስለ አለው የአርያም የልዑል ስፍራ ምትክ በምድር ላይ ከፍተኛ አርያምን (ሰማይን) ሆነሽ የተገኘሽ አንቺ ነሽ፤” ያለው ለዚህ ነው። እኅታቸው ስለሆነች ወደዷት፥ ማኅደረ መለኰት በመሆኗ ደግሞ ሰገዱላት።
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም፡- ሰማያውያን ዘመዷቿ ቅዱሳን መላእክት እና ምድራውያን ዘመዷቿ በሊባኖስ ተራራ በአንድ መሰብሰባቸው ምሳሌነት አለው።ምሳሌነቱም ለቤተክርስቲያን ነው፤ምክንያቱም ፡-ቤተ ክርስቲያን፡-በምድር ያሉ ቅዱሳን ምእመናን እና በሰማይ የሚኖሩ ቅዱሳን አንድነት ናትና።የዚህ ሁሉ ምክ ንያት ደግሞ እመቤታችን ናት፥ እርሷ ከዚህም በላይ ናት።አምላክ ከሰማይ ወርዶ፥ በማኅፀኗ አድሮ፥ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመወለዱ፥ አምላክን እና ሰውን በተዋህዶ ያገናኘች እመቤት ናት። አሁንም በአማላጅነቷ ሰውን እና አምላክን ታገናኛለች። የቅድስት ሐና እና የቅዱስ ኢያቄም ዘመዶች፥ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፥ ተአምራቱ ንም እያደነቁ በደስታ እና በሐሴት ሰባት ቀን ሰነበቱ።
ለግንቦት ልደታ የተሠራው ቀለም (ቃለ እግዚአብሔር)፥ እመቤታችንን፡- “ኦ ማርያም፡- መንክር ልደትኪ፥ ወዕፁብ ግብርኪ፤ ማርያም ሆይ፥ ልደትሽ ድንቅ፥ ሥራሽም ዕፁብ ነው፤” ይላታል። “ይትባረክ እግዚአብሔር ወይትአ ኰት ስሙ፤ ኪያኪ ሠናይተ ዘፈጠረ ለቤዛ ብዙኃን፤ እስመ መሠረት አንቲ ለሕይወተ ኵሉ ዓለም፤ ማርያም እምነ ወእሙ ለእግዚእነ ሰአሊ በእንቲአነ። ለብዙዎች ድኅነት(መዳን) ምክንያት እንድትሆኚ፥ መልካሟን አንቺን የፈጠረ እግዚአብሔር ይባረክ፤ (ይመስገን)፤ ስሙም የተመሰገነ ይሁን። ለዓለሙ ሁሉ የሕይወት መሠረት አንቺ ነሽና፤ የጌታችን እናቱ ማርያም እናታችን ስለ እኛ ለምኚልን።” እያለ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፥ እመቤታችንን ደግሞ ክብሯን እያደነቀ፡- አማላጅነቷን ይማጸናል። ስለ ቅዱስ ኢያቄምና ስለ ቅድስት ሐናም የሚናገረው አለ። “ክልኤቱ አዕሩግ እመ በከዩ ብካየ፥ ረከቡ ዘታስተሠሪ ጌጋየ፥ ለወንጌላውያን ኵልነ ዘኮነት ምጕያየ፤ ኢያቄም ወሐና ወለዱ ሰማየ፥ ሰማዮሙኒ አሥረቀት ፀሐየ፤ ምሥራቀ ምሥራቃት ሙፃአ ፀሐይ፥ እግዝእትነ ዘመና ሙዳይ፥ ተወልደት ዮም ዳግሚት ሰማይ። ሁለቱ አረጋውያን (ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና) ልቅሶን ቢያለቅሱ፥ ለሁላችን ለወንጌላውያን መሸሻ (መጠጊያ) የሆነች፥ በደልን የምታስወግድ እና ኃጢአትን የምታስተሠርይ ልጅ አገኙ፤ ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱ፥ ሰማያቸውም ፀሐይን አወጣች፤ (ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስን ወለደች)፤ የምሥራቆች ምሥራቅ እመቤታችን የመና ሙዳይ ናት፤ ለጽርሐ አርያም ሁለተኛ የምትሆን ዳግሚት ሰማይ ዛሬ ተወለደች፤” ይላል።
የእመቤታችን መወለድ ደስታው ለኃጥአን ብቻ ሳይሆን ለጻድቃንም ነው፥ ወንጌልን ለሚሰብኩ ለሐዋርያት ብቻ ሳይሆን ትንቢት ለተናገሩ ነቢያትም ነው። ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ጻድቃን፥ በአዳም ኃጢአት ምክንያት የጽድቃቸውን ዋጋ አጥተው ወደ ሲኦል ወርደዋል። “ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ (እስከ ክርስቶስ) ድረስ ሞት ነገሠ፤” ይላል። ሮሜ፡፭፥፲፬። በዕዳ ለተያዘ ሰው ተስፋ የሚሆነው በዕዳ ያልተያዘ ሰው ነው። መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀን ጀምሮ የጠበቃት እመቤት፥ ቅድስት ድንግል ማርያም፥ ከአዳም ኃጢአት ዕዳ ነፃ ሆና በመፈጠሯ ለአዳም ልጆች ሁሉ ተስፋ ሆናላቸዋለች። አባ ሕርያቆስ፡- “አዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነበርሽ፤” ያለው ለዚህ ነው። እርሷም እንደ እርሱ፥ በእርሱ ኃጢአት የምትያዝ ቢሆን ኖሮ ተስፋው ልትሆን አትችልም ነበር። ነገር ግን በማይመረመር የእግዚአብሔር ጥበብ ከጥንተ አብሶ(ከጥንት የአዳም በደል) የተሰወረች እመቤት ድንግል ማርያም፡ -የሁሉ ተስፋ፥ የሁሉ ደስታ ሆነች። “ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፥ እም ሐና ወኢያቄም፤ ከመ ትቤዙ ነቢያተ ወጻድቃነ፥ አማን ተወ ልደት እመ ብርሃን፤ ከኢያቄምና ከሐና ስለ ተወለደችው፥ ስለ ማርያም ልደት ዛሬ ደስታ ሆነ፤ ነቢያትን እና ጻድቃንን ታድናቸው ዘንድ (በእርሷ ምክንያት ይድኑ ዘንድ) የብርሃን እናቱ በእውነት ተወለደች፤”ይላል።
Comments
Post a Comment