እኛ ..... በትግስት ማሞ
ን’ጎርሰው ሳይኖረን እኖረው ሳይኖረን
ባዶ ተስፋ መሐል መጪውን ሞሽረን
የሰጡንን ቀምሰን ባሉን አሜን ብለን
ባንድዬ ቸርነት አይችሉትን ችለን
ተገፍቶ የማያልቅ ጉድ ዘመን ተሻግረን
ይኸው ዛሬም አለን
ህልማችን መሐል ላይ ስደት ተስሎበት
በልባችን ሙሉ ራስ መውደድ በቅሎበት
ኑሯችን ጫፉ ላይ ፍርሃት ቋጥረንበት
እምኝ ብርቃችን ነው
መዘመን ከሆነ አዎን ዘምነናል ፈሪ ለ’ናቱ ነው መፍራት ይሻለናል
መሰልጠን ከሆነም አዎ ሰልጥነናል ሃገር ምንያደርጋል
ትውልድ ምናባቱ እኔነት መርጠናል
አዎን ሰልጥነናል አዎን ሰይጥነናል
የሰው ሰርግ አድማቂ አጃቢ ሆነናል
ሕይወቱን የጠላ አንድ ሞኝ ምስኪን ሰው ደፋር እስኪመጣ
ተስፋችንን በፍራት ትውልዱን በፍዘት በግፍ የምንቀጣ
ዛሬ በልቶ ማደር የህሊናችንን ሚዛኑን ያሳተን
ተመሳስሎ ኑሮ አጨብጭቦ ሹመት በባርነት ስለት የሚበላልተን የሚዶላልተን
የምንኖር መሳይ የሆነልን መሳይ የምንቆም ሞተን
እንደዚያ ነን እኛ
Comments
Post a Comment