አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር – ክፍል ሁለት

ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ከሞተ በኋላ በ፫፻፲፪ ዓ.ም አርኬላዎስ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ (ፓትርያርክ) ሆኖ በምትኩ ተሾመ፡፡ በዚህ ጊዜ አርዮስ ከክሕደቱ የተጸጸተ መስሎ ወደ ፓትርያርክ አርኬላዎስ ቀረበ፡፡ የአርዮስ ደጋፊዎችም ፓትርያርኩ ከውግዘቱ እንዲፈታው በአማላጅነት በመቅረባቸው፣ አዲሱ ፓትርያርክ የቀድሞውን ፓትርያርክ የተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስን ትእዛዝና አደራ በመዘንጋት አርዮስን ከውግዘቱ ፈታው፡፡ ይባስ ብሎም የቅስና ማዕረግ ሰጥቶ ሾመው፡፡ ሆኖም አርኬላዎስ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሞት ተለየ፡፡ የሰማዕቱን የቅዱስ ጴጥሮስን ቃል ባለመጠበቁ የመቅሠፍት ሞት ነው የሞተው ይባላል፡፡
በአርኬላዎስም ምትክ ስመ ጥሩውና በዘመኑ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ የተጋደለ አባት እለእስክንድሮስ (፫፻፲፪ – ፫፻፳፰ ዓ.ም) በካህናትና ምእመናን ተመርጦ ተሾመ፡፡ እለእስክንድሮስ ወዲያውኑ የአርዮስን የክሕደት ትምህርት በይፋ እየተቃወመ አርዮስን በጥብቅ አወገዘ፡፡ የአርዮስ ደጋፊዎች አርዮስን ከፓትርያርኩ ጋር ለማስማማት አጥብቀው ቢሞክሩም ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ አልበገርም አለ፡፡ አርዮስ ተጸጽቶ፣ ስሕተቱን ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ተናዝዞ ከተመለሰ ጌታ ምልክት ስለሚሰጠው ያንጊዜ እርሱ እንደሚቀበለው ነግሮ አሰናበታቸው፡፡ አርዮስ በበኩሉ በድፍረት የክሕደት ትምህርቱን ማሠራጨት ቀጠለ፡፡ ሕዝቡም ትምህርቱን በቀላሉ እንዲቀበለው የክሕደት ትምህርቱን በግጥምና በስድ ንባብ እያዘጋጀ ያሠራጭ ጀመር፡፡ ያም የግጥም መጣጥፍ ‹ታሊያ› ይባል ነበር፡፡ ትርጕሙም ማዕድ ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ደግሞ ግጥም ማንበብ ስለሚወድና በግጥም መልክ ያነበበውን ስለማይዘነጋው የአርዮስን ትምህርት ለመቀበል ደርሶ ነበር፡፡
ሊቀ ጳጳሱ እለእስክንድሮስም ምእመናን ከአርዮስ የክሕደት ትምህርት እንዲጠበቁ እየዞረ በማስጠንቀቅ ያስተምር ጀመር፡፡ ፓትርያርኩም በ፫፻፲፰ ዓ.ም በእስክንድርያና በአካባቢዋ የሚገኙትን ጳጳሳትና ካህናት ሰብስቦ አርዮስንና ተከታዮቹን በጉባኤ አወገዛቸው፡፡ አርዮስ ግን ከስሕተቱ ባለመመለሱ ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ በ፫፻፳፩ ዓ.ም አንድ መቶ የሚሆኑ የእስክንድርያንና የሊብያን ኤጲስቆጶሳት ሰብስቦ ጉባኤ በማድረግ የአርዮስን ክሕደት በዝርዝር አስረዳቸው፡፡ ሲኖዶሱም ጉዳዩን በሚገባ ከመረመረ በኋላ አርዮስን በአንድ ድምፅ አወገዘው፡፡ አርዮስም በበኩሉ እየዞረ‹‹እለእስክንድሮስ ሰባልዮሳዊ ነው፤ የሰባልዮስን የክሕደት ትምህርት ያስተምራል›› እያለ የሊቀ ጳጳሱን የእለእስክንድሮስን ስም ማጥፋት ጀመረ፡፡ በመሠረቱ ከሰባልዮስ ትምህርት ጋር የሚቀራረበው‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› (ሎቱ ስብሐት) የሚለው የአርዮስ ትምህርት ነው እንጂ ‹‹ወልድ የባሕርይ አምላክ ነው፤ ከአብም ጋር በባሕርይ አንድ ነው (ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ)›› የሚለው ትምህርት አይደለም፡፡
የአርዮስ ትምህርት በእስክንድርያና በመላዋ ግብጽ ብዙም ተቀባይነት ባለማግኘቱ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ወደ ሦርያና አንጾኪያ እየዞረ ቀድሞ ጓደኞቹ ለነበሩትና የእርሱን የክሕደት ትምህርት ለሚደግፉ ጳጳሳት ሁሉ ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ ያለ አግባብ እንዳወገዘውና እንዳባረረው ከመንገሩም በላይ ‹‹እለእስክንድሮስ የሰባልዮስን ትምህርት ያስተምራል›› እያለ ስሙን ያጠፋ ጀመር፡፡ በዚያ የነበሩት የአርዮስ የትምህርት ቤት ጓደኞች ጳጳሳት ለምሳሌ የኒቆምዲያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስና የቂሣርያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ የአርዮስን ሐሳብ ይደግፉ ስለነበር አርዮስ የክሕደት ትምህርቱን እየዞረ እንዲያስተምር ፈቀዱለት፡፡ ከዚህም በላይ ደፍረው ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ አርዮስን እንዲቀበለው ጠየቁለት፡፡ ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ ግን ይህንን ጥያቄ አልተቀበለውም ነበር፡፡ እንደውም እለእስክንድሮስ በበኩሉ የአርዮስን የክሕደት ትምህርት በመቃወምና በማውገዝ ብዙ ደብዳቤዎችን በመላዋ ግብጽና በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ያስተላልፍ ጀመር፡፡
በአርዮስ ደጋፊ በኒቆምዲያ ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ አሳሳቢነትና ሰብሳቢነት በ፫፻፳፪ እና ፫፻፳፫ ዓ.ም በተከታታይ ሁለት ጉባኤያትን አድርገው የአርዮስ ትምህርት ትክክለኛ መሆኑን በማብራራትና ‹‹የአርዮስ ሃይማኖት ትክክል ስለሆነ መወገዝ አይገባውም›› በማለት የእለእስክንድሮስን ውግዘት በመሻር ለአርዮስ ፈረዱለት፡፡ አርዮስም ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ያንኑ የክሕደት ትምህርቱን በስፋት ያስተምር ጀመር፡፡ በአርዮስ ክሕደት ምክንያት የተነሣው ውዝግብ በመላው የክርስትና አህጉር ሁሉ በተለይም በምሥራቁ የሮም ግዛት በመሠራጨቱ ቤተ ክርስቲያንና የሮም ግዛት በሙሉ እጅግ ታወኩ፡፡ ጳጳሳትና መምህራን እርስበርሳቸው ይነታረኩ ጀመር፡፡ በዚህም ሰላም ጠፍቶ በዚያው ወቅት የመላ የሮም ንጉሠ ነገሥት መንግ ሥት ብቸኛ ቄሣር የሆነውን ታላቁን ቈስጠንጢኖስ እጅግ አሳሰበው፡፡ ንጉሠ ነገሥት ቈስጠንጢኖስ በመላ ግዛቱ ሰላም እንዲሰፍን በመሻቱ ውዝግቡን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማብረድ መልእክተኞችን ደብዳቤ አስይዞ ወደየጳጳሳቱ ይልክ ጀመር፡፡ በደብዳቤውም የቃላት ጦርነት እንዲያቆሙና በሰላም እንዲኖሩ ይጠይቅ ነበር፡፡
ለዚህም መልእክት ጉዳይ ሽማግሌ የነበረውን በስፔን የኮርዶቫ ጳጳስ ኦስዮስን ወደ እስክንድርያ ደብዳቤ አስይዞ ላከው፡፡ ኦስዮስም በአንድ በኩል ከእለእስክንድሮስና ከግብጽ ኤጲስቆጶሳት ጋር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከአርዮስና ከእርሱ ደጋፊዎች ጋር ተወያይቶ በሁለቱ መካከል የነበረውን ልዩነት በሚገባ ከመረመረ በኋላ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ቈስጠንጢኖስ ተመልሶ ነገሩ ከባድ የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ የመላው ሕዝበ ክርስቲያን ጳጳሳት የሚገኙበት ታላቅ ጉባኤ ተጠርቶ ውዝግቡ በጉባኤ ታይቶ ቢወሰን እንደሚሻል ለንጉሠ ነገሥቱ ምክር ሰጠ፡፡ ታላቁ ቈስጠንጢኖስም ምክሩን ተቀብሎ የመላው አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፋዊ ሲኖዶስ እንዲደረግ አዋጅ ነገረ፡፡ ጉባኤውም የቢታንያ አውራጃ ከተማ በሆነችው በኒቅያ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ለጉዞና ለኑሮ የሚያስፈልገው ወጪ ሁሉ ከመንግሥት ካዝና እንዲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡
ስለዚህም ቈስጠንጢኖስ በነገሠ በሃያ ዓመቱ በ፫፻፳፭ ዓ.ም በሮም ግዛት ውስጥ የነበሩት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስቆጶሳትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰበሰቡ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ እያንዳንዱ ኤጲስቆጶስ ሁለት ቀሳውስትንና ሦስት ምእመናንን (ሊቃውንትን) ይዞ እንዲመጣ ንጉሡ በፈቀደው መሠረት ብዙ ቀሳውስትና ምእመናን (ሊቃውንት) በጉባኤው ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ ለጉባኤው የተሰበሰቡት አባቶችም ፫፻፲፰ ያህሉ ነበር፡፡ በጉባኤው የተሰበሰቡትን አባቶች ቍጥር የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ከፊሎቹ ከፍ፣ ሌሎቹ ደግሞ ዝቅ አድርገው ይጽፋሉ:: ለምሳሌ የቂሣርያው አውሳብዮስ ፪፻፶ ነበሩ ሲል፣ ቴዎዶሬት ደግሞ ፪፻፸ ነበሩ ይላል፡፡ እንደዚሁም ሶቅራጥስ ፫፻፤ ሶዞሜን ደግሞ ፫፻፳ ነበሩ ይላሉ፡፡
በጉባኤው የተሰበሰቡት አባቶች በሕይወታቸው ንጽሕናና ቅድስና መሰል የሌላቸው፣ በሃይማኖታቸውም የሐዋርያትን ፈለግ የተከተሉ ነበሩ፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር በገቢረ ተአምራት ከፍ ያለ ዝና ያላቸው ነበሩ፡፡ በስብሰባውም ላይ ሃያ አርዮሳውያን ኤጲስቆጶሶች፣ የተወሰኑ አርጌንሳውያንና የፍልስፍና ምሁራን ተጠርተው መጥተው ነበር፡፡ የጉባኤው የክብር ፕሬዝዳንት ንጉሠ ነገሥቱ ታላቁ ቈስጠንጢኖስ ሲሆን፣ ጉባኤውን በሊቀ መንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት ነበሩ፡፡ እነዚህም፡- የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ እለእስክንድሮስ፣ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ኤዎስጣቴዎስ እና የኮርዶቫው (የእስፔኑ) ጳጳስ ኦስዮስ ነበሩ፡፡ ከጉባኤው ተካፋዮች መካከል እጅግ የታወቁ ምሁራን ነበሩ፡፡
ከእነዚህም ጥቂቶቹ እጅግ የተማረ፣ ንግግር ዐዋቂና ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ቀናተኛ የነበረው፣ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ዲያቆን ሆኖ ለሊቀ ጳጳሱ ለእለእስክንድሮስ እንደ አፈ ጉባኤ የነበረው አትናቴዎስና ስመ ጥር የነበረው የቂሣርያው አውሳብዮስ ነበሩ፡፡ እንደዚሁም በዘመነ ስደት ጊዜ ለሃይማኖታቸው ብዙ ሥቃይ የተቀበሉ፣ ዓይናቸው የጠፋ፣ እጅ ወይም እግራቸው የተቆረጠ በቅድስናቸው የታወቁ አባቶችም ነበሩ፡፡ ከዚህም ሌላ በምንኵስና እና በብሕትውና ኑሯቸው እጅግ የታወቁ፣ የዛፍ ሥርና ቅጠል ብቻ በመብላት ይኖሩ የነበሩ፣ ተአምራትን በማድረግ በክርስቲያኖች ዘንድ እጅግ የተከበሩ አባቶች ነበሩ፡፡
ጉባኤው በአብዛኛው የተካሔደው በኒቅያ ከተማ በምትገኘው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እዚያው ኒቅያ በሚገኘው በንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት አዳራሽ ይካሔድ እንደነበር ይነገራል፡፡ ጉባኤውም በሦስት ቡድን የተከፈለ ነበር፤ ይኸውም የመጀመሪያው የኦርቶዶክሳውያን፣ ሁለተኛው የአርዮሳውያን፣ ሦስተኛው ደግሞ የመንፈቀ አርዮሳውያን ቡድን ሲሆን፣ በመጀመሪያው ቡድን የነበሩት ኦርቶዶክሳውያን መሪዎችም የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ እለእስክንድሮስ፣ ሊቀ ዲያቆኑ አትናቴዎስ፣ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ኤዎስጣቴዎስ፣ የኮርዶቫው (የእስፔኑ) ኤጲስቆጶስ ኦስዮስ፣ የአንኪራው (ዕንቆራው) ኤጲስቆጶስ ማርሴሎስ ወዘተ. ነበሩ፡፡
ከእነዚህም ሁሉ በክርክሩ ወቅት ጠንካራና ከባድ ክርክር ይከራከር የነበረውና፣ ለተቃዋሚዎቹ አፍ የሚያስይዝ ምላሽ ይሰጥ የነበረው የእስክንድርያው ሊቀ ዲያቆን አትናቴዎስ ነበር፡፡ በሁለተኛው ቡድን የነበሩትም አርዮስና የንጉሡ ወዳጅ የነበረው የኒቆምዲያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ፣ የኒቅያው ኤጲስቆጶስ ቴኦግኒስ፣ የኬልቄዶን ኤጲስቆጰስ ማሪስና የኤፌሶን ኤጲስቆጶስ ሜኖፋንቱስ ነበሩ፡፡ አርዮስ ግን ተከሳሽ ስለነበረ በየጊዜው በጉባኤው እየተጠራ መልስ ይሰጥ ነበር እንጂ የሲኖዶሱ ተካፋይ አልነበረም፡፡ ሦስተኛው ቡድን የመንፈቀ አርዮሳውያን (የመሀል ሰፋሪዎች) ቡድን ሲሆን፣ የእነርሱ ወኪልም የታወቀው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የቂሣርያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ ነበር፡፡ ይህ ሰው መንፈቀ አርዮሳዊ ሆኖ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተመልሷል፡፡
ይቆየን

Comments

Popular posts from this blog

የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል። መዝሙር ፻፲፩፥፮

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም

ዘመነ ፍሬ› ደግሞ ‹የፍሬ ወቅት፣ የፍሬ ዘመን፣ የፍሬ ጊዜ›