ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል ሁለት
፫. የተሰወረ ምሥጢር እንዲገለጥልን
በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ነገሥታት ራእይ በማሳየት ምሥጢርን ይሰውርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የግብጹን ፈርዖን፣ የባቢሎኑን ናቡከደነፆርና ብልጣሶርን መጥቀስ ይቻላል (ዘፍ. ፵፩፥፲፬-፴፮፤ ዳን. ፬፥፱፣ ፭፥፬)፡፡ እነዚህ ነገሥታት በግል ሕይወታቸውም ኾነ በአጠቃላይ ለሕዝቡ ትምህርት በሚኾን መልኩ ወደ ፊት ሊፈጸም የሚችል ራእይ ቢያዩም ቅሉ ራእዩን በትክክል ተረድተው እንዲህ ይኾናል የማለት ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህም በዘመናቸው ይኖር የነበሩትን ነቢያት ሱባዔ ገብተው የሕልማቸውን ትርጉም እንዲነግሩአቸው ይማጸኑ ነበር፡፡
ነቢያትም ሱባዔ በመግባት ነገሥታቱ ያዩትን የምሥጢረ ሥጋዌ ነገርና የመንግሥታቸውን አወዳዳቅ ገልጠው ያስረዱ ነበር (ዳን. ፭፥፳፰)፡፡ እንደዚሁም ቅዱሳን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢር ሲከደንባቸው የራእዩ ምሥጢርና ትርጕም እንዲገለጥላቸው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ኾነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዕዝራ የመጻሕፍትን ምሥጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል (መዝ. ፰፥፩)፡፡ ከዚህ ቀጥለን የቀደምት አበውን ሱባዔና ያስገኘላቸውን ጥቅም በአጭር በአጭሩ እንመለከታለን፤
ሱባዔ አዳም
አዳም ትንቢት በመናገርና ሱባዔ በመቍጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በተድላና በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ በማፍረሱና የፈጣሪውን ቃል በመጣሱ ያለ ምንም ትካዜና ጕስቁልና ከሚኖርበት ዔደን ገነት ተባርሯል (ዘፍ. ፫፥፳፬)፡፡ እርሱም ፈጣሪው እንዲታረቀው፣ በዐይነ ምሕረት እንዲጐበኘው፣ ቅዝቃዜው ሰውነትን ከሚቈራርጥ ባሕር ውስጥ በመግባት ለሠላሳ አምስት ቀን (አምስት ሱባዔ) ሱባዔ ገብቷል፡፡ በባሕርዩ የሰውን ልጅ እንግልት የማይወድ መሐሪው እግዚአብሔርም የአዳምን ፍጹም መጸጸት ተመልክቶ ‹‹በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ፤ በአምስት ቀን ተኩል ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ብሎ የድኅነት ተስፋ ሰጠው፡፡
አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቈጥር፣ አዳምም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለ ነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቈጠረ‹‹የተናገረውን የማያስቀር፣ የማያደርገውን የማይናገር ጌታዬ፤ እነሆ ‹አድንሃለሁ› ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤›› እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸሩ አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ‹‹ተንሥኡ ለጸሎት፤ ለጸሎት ተነሡ፡፡ ሰላም ለኵልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይኹንን!›› በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡
ሱባዔ ሔኖክ
ጻድቁ ሔኖክ የያሬድ ልጅ ሲኾን፣ በትውልድ ከአዳም ሰባተኛ ነው፡፡ እርሱም በሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ቤት ንብረቱን በመተው በሱባዔና በትሕርምት እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ ፍጹም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው በመኾኑም በብሉይ ኪዳንም ኾነ በሐዲስ ኪዳን የመልካም ግብር ባለቤት መኾኑ ተመስክሮለታል፡፡ ‹‹ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዘፍ. ፭፥፳፪)፡፡ ይህም በመኾኑ እግዚአብሔር የሱባዔውን ዋጋ ቅዱስ መንፈሱን በረድኤት ስለ አሳደረበት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔ ቈጥሯል፡፡ በሰማይ ተሰውሮ ሳለ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አመላለስ (ዑደት) የሚተርክ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል (ዘፍ. ፭፥፳፩-፳፬፤ ሔኖክ ፩፥፱፤ ይሁዳ፣ ቍ. ፲፬)፡፡
ሱባዔ ሔኖክ የሚባለው ነቢዩ ሔኖክ በመሥፈርት የቈጠረው ሱባዔ ነው፡፡ መሥፈርቱ (ማባዣ ቍጥሩ) 35 ሲኾን 35 በ19 ሲበዛ ውጤቱ 685 ዓመት ይኾናል፡፡ 685ን በ12 ስናባዛው ደግሞ 7980 ይኾናል፡፡ ይኸውም ሐሳብ የሚያስረዳው ስለ ክርስቶስ ምጽአት ነው፡፡ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ 7509 ይኾናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በ5500 ዓመት ላይ 2009 ዓመትን መደመር ነው፡፡ በነቢዩ ሔኖክ አቈጣጠር መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ በ7980 ይኾናል፡፡ ከላይ ሔኖክ የቀመረውን ቍጥር ይዘን ከ7980 ዓመት ላይ አሁን ያለንበትን ዘመን (7509) ስንቀንስ 471 ዓመት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሔኖክ ሱባዔ መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ ሊኾን 471 ዓመት ይቀረዋል ማለት ነው፡፡
ሱባዔ ነቢያት
እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ቀደምት ነቢያት በተነሡበት ዘመን ቅደም ተከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መኾንና ዳግም መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፤ ሱባዔም ቈጥረዋል (መዝ. ፵፱፥፫፤ ኢሳ. ፯፥፲፬፤ ዘካ. ፲፫፥፮፣ ፲፬፥፩)፡፡ የአንዱ ነቢይ ትንቢታዊ ንግግርና ሱባዔ በአነጋገርና በአቈጣጠር ከሌላኛው ነቢይ ይለያል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ትንቢቱን ሲያናግር፣ ምሳሌውን ሲያስመስል ጐዳናው ለየቅል በመኾኑ ነው፡፡ ‹‹ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤›› እንዲል (ዕብ. ፩፥፩)፡፡ የአቈጣጠር ስልታቸውና የሱባዔ መንገዳቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን አንድ ነው፡፡
ሱባዔ ዳንኤል
ነቢዩ ዳንኤል ምድቡ ከዐበይት ነቢያት ነው፡፡ እስራኤል ወደ ባቢሎን ሲማረኩ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ወርዷል፡፡ እርሱም ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔም ቆጥሯል፡፡ ከትንቢቶቹ መካከልም፡- ‹‹ሰብአ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ፤ ሰባ ሰንበት ወገኖችህን ቅጠራቸው፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ከ490 ዓመት በኋላ ሰው መኾኑን የሚያመለክት ትንቢት ነው፡፡ እንደዚሁም ‹‹እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ትትሐነጽ መቅደስ ወእምዝ ትትመዘበር፤ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ መቅደስ ትታነጻለች፤ በኋላም ትፈርሳለች፤›› በማለት የብሉይ ኪዳንን ማለፍና የሐዲስ ኪዳንን መመሥረት ተናግሯል፡፡ የዳንኤል የሱባዔ አቈጣጠር ስልቱም በዓመት ሲኾን ይኸውም ሰባቱን ዓመት አንድ እያሉ መቍጠር ነው፡፡ ይህም ‹ሱባዔ ሰንበት› ይባላል፡፡ ዳንኤል ሱባዔ ከቈጠረበትና ትንቢት ከተናገረበት ጊዜ ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ተወለደበት ድረስ 490 ዓመት ይኾናል፡፡ መሥፈርቱ (ማባዣው) ሰባት ስለኾነ ሰባትን በሰባ ብናባዛው 490ን እናገኛለን፡፡ ይኸውም ነቢዩ ሱባዔ ከቈጠረና ትንቢት ከተናገረ ከ490 ዓመት በኋላ ክርስቶስ መወለዱን ያመለክታል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳን ነቢያት አካሔዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ሱባዔ ገብተው በትሕርምት በመኖራቸው ድንቅ የኾነውን የክርስቶስን ልደትና ዳግም ምጽአት ለመተንበይ ችለዋል፡፡ ሱባዔ መግባት የራቀውን የማቅረብ፣ የረቀቀውን የማጉላት ጸጋን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጥበብ መኾኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
ሱባዔ ዳዊት
ነቢዩ ዳዊት ከእስራኤል ነገሥታት ዅሉ ታላቅና ተወዳጅ ንጉሥ ነበር፡፡ ዘመነ መንግሥቱ 1011 – 971 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደ ነበር ይታመናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ልበ አምላክ እንደ መኾኑ ብዙ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሱባዔ ቈጥሯል፡፡ ይኸውም ‹ቀመረ ዳዊት› በመባል ይታወቃል፡፡ ‹‹እስመ ዐሠርቱ ምእት ዓመት በቅድሜከ ከመ ዕለት እንተ ትማልም ኀለፈት፤ ሺሕ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን ናት፤›› (መዝ. ፹፱፥፬) የሚለውን ኃይለ ቃል መምህራን ሲቈጥሩት 1140 ዓመት ይኾናል፡፡ ይኸውም በጌታ ዘንድ 1140 ዓመት እንደ አንድ ቀን እንደ ኾነ ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም ለዳዊት ሱባዔ መቍጠሪያ (መሥፈሪያ) ኾኖ አገልግሏል፡፡ 1140 በ7 ሲባዛ 7980 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በ7980 ዓመት ክርስቶስ ዳግም እንደሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡
ይቆየን
Comments
Post a Comment